





























Hadeeth Cards
Da'wa cards that highlight great meanings from the noble prophetic hadiths in a simple style and attractive display that helps the Muslim to have a deeper understanding of his religion in an easy way
All
ከአቡ ዋቂድ አል-ለይሢይ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፉት: "የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ወደ ሑነይን የወጡ ጊዜ 'ዛቱ አንዋጥ' በምትባል የአጋርያን ዛፍ በኩል አለፉ። በርሷ ላይ (በረከትን በመፈለግ) መሳሪያዎቻቸውን ያንጠለጥሉባት ነበር። ሶሐቦችም 'የአላህ መልክተኛ ሆይ! ለነርሱ ‹ዛቱ አንዋጥ› እንዳላቸው ለኛም (የምናንጠለጥልበት) ‹ዛቱ አንዋጥ› አድርግልን።' አሉ። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ አሉ 'ለአላህ ጥራት ተገባው! ይህ (የተናገራቹት) የሙሳ ህዝቦች {ለእነርሱ አማልክት እንዳላቸው ለእኛም አምላክን አድርግልን።} [አል አዕራፍ: 138] ብለው እንደተናገሩት ነው። ያ ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታዬ እምላለሁ! ከናንተ በፊት የነበሩትን ህዝቦች መንገድ ትከተላላችሁ።'"
ቲርሚዚና አሕመድ ዘግበውታል።የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ወደ ሑነይን ወጡ። ሑነይን: በጧኢፍና መካ መካከል የሚገኝ ሸለቆ ነው። ከርሳቸውም ጋር የሚጓዙ በቅርብ ወደ ኢስላም የገቡ የተወሰኑ ሶሐቦች ነበሩ። "ዛቱ አንዋጥ" ማለትም የመንጠልጠያ ባለቤት በምትባል ዛፍ በኩል አለፉ። ዛፊቱ አጋርያን ያልቋትና መሳሪያዎቻቸውንና ሌሎች ነገሮችንም በረከትን በመፈለግ የሚያንጠለጥሉባት ዛፍ ነበረች። ከመልክተኛው (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ለነርሱ በረከትን ለመፈለግ መሳሪያዎቻቸውን የሚያንጠለጥሉበት የርሷ አምሳያ ዛፍ እንዲያደርጉላቸው ፈለጉ። ይህም የሚፈቀድ ነገር ስለመሰላቸው ነው። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ይህንን ንግግራቸው እያወገዙ አላህን በማላቅ ተስቢሕ አደረጉ። ይህ ንግግር የሙሳ ህዝቦች {ለእነርሱ አማልክት እንዳላቸው ለእኛም አምላክን አድርግልን።} በማለት ለሙሳ የተናገሩትን ንግግር እንደሚመስልም ተናገሩ። የሙሳ ህዝቦች ጣኦት የሚያመልክን በተመለከቱ ጊዜ አጋርያን ጣኦት እንዳላቸው ለነርሱም ጣኦት እንዲኖራቸው ፈለጉ። ይህ ግን የነርሱን መንገድ መከተል ነው። ቀጥለውም ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ይህ ህዝብ የየሁዶችንና የክርስቲያኖችን መንገድ እንደሚከተልና የነርሱን ድርጊት እንደሚፈፅም በማስጠንቀቅ መልኩ ተናገሩ።
ከኢብኑ ዓባስ (ረዲየሏሁ ዐንሁማ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው: "አንድ ሰውዬ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ዘንድ መጣና በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ አውርቷቸው 'የአላህና የእርሶ መሻት ሆነ።' አለ። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) 'ለአላህ ቢጤ አደረግከኝን? የብቸኛው አላህ መሻት ሆነ! በል!' አሉት።"
ኢብኑ ማጀህ፣ ነሳኢ በኩብራ ውስጥ፣ አሕመድ ዘግበውታል።አንድ ሰውዬ ወደ ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ዘንድ በመምጣት የግሉን ጉዳይ አወራቸውና ከዚያም "የአላህና የእርሶ መሻት ሆነ።" አላቸው። ነቢዩም (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ይህ ንግግሩን አወገዙት። የፍጡርን መሻት ከአላህ መሻት ጋር አቆራኝቶ መናገር ሙስሊም ሊለው የማይፈቀድለት ትንሹ ሺርክ መሆኑን ተናገሩ። ቀጥለውም ትክክለኛው አባባል "የብቸኛው አላህ መሻት ሆነ።" ማለቱ እንደሆነ ጠቆሙት። አላህን በመሻቱ መነጠል እንጂ በማንኛውም ማቆራኛ ቃላት የአንድንም አካል መሻት ከአሏህ ጋር ማቆራኘት የለበትም።
ከአማኞች እናት ዓኢሻ (ረዲየሏሁ ዐንሃ) - አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና - እንደተላለፈው እንዲህ አለች: "እቃ ክፍሌን (የተንቀሳቃሽ እንስሳ) ምስል ባለበት መጋረጃ ሸፍኜው ሳለ የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እኔ ዘንድ መጡ። የተመለከቱት ጊዜም ፊታቸው ተለዋውጦ ቀደዱትና እንዲህም አሉ 'ዓኢሻ ሆይ! የትንሳኤ ቀን አላህ ዘንድ ከሰዎች ሁሉ እጅግ ብርቱ ቅጣት የሚቀጡት እነዚያ በአላህ ፍጥረት የሚፎካከሩት ናቸው።'" ዓኢሻም እንዲህ አለች "ቆርጠነው በርሱ አንድ ትራስ ወይም ሁለት ትራስ አደረግንበት።"
ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ቤታቸው ዓኢሻ (ረዲየሏሁ ዐንሃ) - አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላትና - ዘንድ ሲገቡ እቃ የምታስቀምጥበትን ትንሽዬ ክፍል ነፍስ ያላቸው ምስሎች ባለበት መጋረጃ ሸፍናው አገኟት። የፊታቸው ቀለምም ለአላህ ብለው በመቆጣታቸው ምክንያት ተለዋውጦ መጋረጃውን አወለቁት። እንዲህ አሉ: የትንሳኤ ቀን ከሰዎች ሁሉ እጅግ ብርቱ ቅጣት የሚቀጡት የአላህን ፍጥረት አስመስለው ምስል የሚያደርጉት ናቸው። ዓኢሻም እንዲህ አለች: እርሱን አንድ ትራስ ወይም ሁለት ትራስ አደረግነው።
ከአቡ ሁረይራ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ አሉ: "አላህ እንዲህ አለ: የአደም ልጅ አስተባበለኝ ይህ ለርሱ አይገባም ነበር! ሰደበኝም ይህም ለርሱ አይገባም ነበር! እኔን ማስተባበሉማ ‹መጀመሪያ እንደፈጠረኝ (የትንሳኤ ቀን) አይመልሰኝም› ማለቱ ነው። በኔ ላይ እርሱን (የትንሳኤ ቀን) ከመመለስ ይልቅ መጀመሪያ መፍጠሩ ቀላል አይደለምን?። እኔን መስደቡማ ‹አላህ ልጅን ያዘ!› ማለቱ ነው። እኔ አንድ ነኝ፣ የሁሉ መጠጊያም ነኝ፣ አልወልድም፣ አልወለድም፣ ለኔም አንድም ቢጤ የለኝም።"
ቡኻሪ ዘግበውታል።ነቢዩ ( የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በዚህ ሐዲሠል ቁድስ ውስጥ አላህ ስለአጋርያንና ከሀዲዎች እነርሱ እንደሚያስተባብሉት፣ በጉድለትና ነውሮች እንደሚገልፁትና ይህም ለነርሱ እንደማይገባ መናገሩን ገለፁ። አላህን ማስተባበላቸውም: አላህ ካልነበሩበት መጀመሪያ የፈጠራቸው ሲሆን ከሞቱ በኋላም ድጋሚ እንደማይመልሳቸው መሞገታቸው ነው። ምንም እንኳ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ስለሆነ መጀመሪያ መፍጠርም ይሁን ወደነበሩበት መመለስ ከአሏህ አንፃር እኩል ቢሆንም መጀመሪያ ካልነበሩበት የፈጠረ አምላክ እነርሱን በመመለስ ላይም ቻይ መሆኑን ነገራቸው። አላህን መስደባቸውም: ለርሱ ልጅ አለው ማለታቸው ነው። በነርሱ ላይም እርሱ አንድ፣ በስሞቹ፣ በባህሪያቱና በድርጊቱ በሁሉም ምሉዕነት ብቸኛ የሆነ፤ ከሁሉም ጉድለትና ነውርም የጠራ፤ ከማንም የማይፈልግ፤ እያንዳንዱ ሁሉ ግን ወደርሱ የሚፈልጉ የሆነ መጠጊያ፤ ለአንድም አካል ወላጅ ያልሆነ፤ ለአንድም አካል ልጅ ያልሆነ፤ ከአምሳያ ወይም ቢጤ አንዳችም የሌለኝ ነኝ። በማለት መለሰላቸው።
ከአቡ ሁረይራ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) -አላህ መልካም ስራቸውን ይውደድላቸውና- እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: "የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል: 'አላህ እንዲህ ብሏል: ‹የኔን ወዳጅ (ወሊይ) ጠላት አድርጎ የያዘን ሰው በርግጥም ጦርነት እንዳወጀኩበት አሳውቄዋለሁ። ባሪያዬ ግዴታ ካደረግኩበት በበለጠ ወደ እኔ ተወዳጅ በሆነ በአንዳችም ነገር አይቃረብም። ባሪያዬ ወደ እኔ በትርፍ ስራዎች ከመቃረብ አይወገድም የምወደው ቢሆን እንጂ፤ የወደድኩትም ጊዜ የሚሰማበት መስሚያው እሆነዋለሁ፣ የሚያይበት መመልከቻ እሆነዋለሁ፣ የሚጨብጥበት እጅ እሆነዋለሁ፣ የሚራመድበት እግር እሆነዋለሁ፣ ቢጠይቀኝ እሰጠዋለሁ፣ ከኔ ጥበቃ ከፈለገ እጠብቀዋለሁ። እኔ ከማደርገው መካከል የሙእሚን ነፍስን ለመውሰድ እንደማመነታው በአንዳችም ነገር አላመነታሁም። እርሱ ሞትን ይጠላል እኔ ደግሞ እርሱን መጉዳት እጠላለሁ።›'"
ቡኻሪ ዘግበውታል።ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) በሐዲሠል ቁድስ አላህ እንዲህ እንዳለ ተናገሩ: ከወዳጆቼ መካከል አንድን የኔን ወዳጅ ያወከውና ያስቆጣው ከኔ ጋር ጠላት እንደሆነ አውጄያለሁም አሳውቄዋለሁም፤ "ወሊይ" (የአላህ ወዳጅ) የሚባለው: አላህን ፈሪ አማኝ ነው። አንድ ባሪያ ባለው ኢማንና አላህን ፈሪነት ልክ የአላህ ወዳጅነት ይኖረዋል። አንድ ሙስሊም አላህ ግዴታ ያደረገበትነን ትእዛዛትን መፈፀምና ክልክሎችን መተው ወደ አላህ እንደሚያቃርበው ምንም ነገር ወደ ጌታው ተወዳጅ በሆነ ነገር አይቃረብም። አንድ ሙስሊም ወደ ጌታው ከግዴታዎች ጋር በትርፍ ስራዎች ከመቃረብ አይወገድም የአላህን ውዴታ የሚያገኝ ቢሆን እንጂ፤ አላህ የወደደው ጊዜ በነዚህ አራት አካላቱ ላይ ለርሱ አጋዥ ይሆነዋል። በመስሚያው ያግዘዋል። አላህን ከሚያስደስት ነገር ውጪ ሌላ ምንም አይሰማም። በመመልከቻው ያግዘዋል። አሏህ እንዲታይ የሚወደውንና የሚያስደስተውን ነገር እንጂ ሌላ አይመለከትም። በእጁም ያግዘዋል። በእጁ አላህን ከሚያስደስት ነገር በቀር አይሰራም። በእግሩም ያግዘዋል። አላህን ወደሚያስደስት ነገር ካልሆነ በቀር አይራመድም። መልካም ነገር ወዳለበት ካልሆነ በቀር አይሮጥም። ከዚህም ጋር አላህን አንዳች ነገር ከጠየቀው አላህ የጠየቀውን ይሰጠዋል፤ ተማፅኖውንም የሚሰማው ይሆናል። በአላህ ጥበቃን ካስፈለገውና የአሏህን ከለላ ፈልጎ ከተጠጋ ጥራት የተገባው አላህም ከሚፈራው ነገር ይጠብቀዋል። ቀጥሎም አላህ እንዲህ አለ: የሙእሚንን ነፍስ ስወስድ ለርሱ በማዘን እንደማመነታው እኔ ከምሰራው በአንዳችም ነገር አላመነታሁም። ምክንያቱም እርሱ ካለው ህመም አንፃር ሞትን ይጠላል። አላህ ደግሞ ሙእሚንን የሚያሳምም ነገር ይጠላል።
ከአቡ ሁረይራ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: «የአላህ መልክተኛ (ሶለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል: "በሰዎች ውስጥ ሁለት ነገሮች አሉ፤ እነርሱም ክህደት ናቸው። በዘር መተቸትና በሞተ ላይ ሙሾ ማውረድ ናቸው።"»
ሙስሊም ዘግበውታል።ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና በሰዎች መካከል ስለሚገኙ ሁለት የከሃዲያን ስራዎችና የድንቁርና ዘመን ስነ ምግባሮች ተናገሩ። እነርሱም: የመጀመሪያው: ሰዎችን በዘራቸው መተቸት፣ ማሳነስና በዘር እነርሱ ላይ መኩራራት ነው። ሁለተኛው: በመከራ ወቅት የአላህን ውሳኔ በማማረር ድምፅን ከፍ ማድረግ ወይም ከትእግስት ማጣት ብዛት ልብስን መቅደድ ነው።
ከአቡ ሁረይራ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው: የአላህ መልክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) እንዲህ ብለዋል: "ድሃ ማን እንደሆነ ታውቃላችሁን?" ሶሐቦችም: "እኛ ዘንድ ድሃ ማለት ዲርሀምና መጠቃቀሚያ እቃ የሌለው ሰው ነው።" አሉ። እርሳቸውም: "በኡመቴ ውስጥ ድሃ ማለት የትንሳኤ ቀን ሶላት፣ ፆም፣ ዘካ ይዞ የሚመጣ ነው። ነገር ግን ሲመጣ ይህንን ሰድቧል፣ ይህንን በዝሙት ዘልፏል፣ የዚህን ገንዘብ በልቷል፣ የዚህን ደም አፍስሷል፣ ይህንን መትቷል። ለዚህኛውም (ለተበዳዩ) ከመልካም ስራው ይሰጠዋል። ለዚያኛውም ከመልካም ስራው ይሰጠዋል። በርሱ ላይ ያለበት ሀቅ ተፈርዶ ሳይጠናቀቅ መልካም ስራው ካለቀ ደሞ ከነርሱ ወንጀል እየተወሰደ በርሱ ላይ ይጫንበትና ከዚያም እሳት ውስጥ ይጣላል።" አሉ።
ሙስሊም ዘግበውታል።ነቢዩ (የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ባልደረቦቻቸውን: ድሀ ማን እንደሆነ ታውቃላችሁን? ብለው ጠየቁ። እነርሱም: በመካከላችን ድሃ የምንለው ገንዘብና እቃ የሌለውን ነው አሉ። እርሳቸውም: በኡመቴ ውስጥ የትንሳኤ ቀን ድሃ የሚባለው እንደ ሶላት፣ ዘካና ፆም የመሰሉ መልካም ስራዎችን ይዞ የሚመጣ ነው። (ነገር ግን) ሲመጣም ይህንን ሰድቦታል፣ ይህንን በክብሩ ዘልፎታል፣ የዚህን ገንዘብ በልቶ ክዶታል፣ የዚህን ደም አፍስሶ በድሎታል፣ ይህንን ደግሞ ደብድቦ አዋርዶታል። ለተበዳዮቹም ከምንዳዎቹ እየተቀነሰ ይሰጣቸዋል። እርሱ ላይ ያሉት ሐቆችና በደሎች ተፈርዶ ሳይጠናቀቅ መልካም ስራው ከተጠናቀቀ ከተበዳዩ ወንጀል ይወሰድና ወደ በዳዩ መዝገብ ይደረጋል። ከዚያም ምንም መልካም ስራ ስላልቀረው እሳት ውስጥ ተወርውሮ ይጣላል።
ከአቡ ሁረይራ (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: «የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና እንዲህ ብለዋል: "የወርቅና የብር ባለቤት ሆኖ ሐቃቸውን የማይወጣ ሰው የትንሳኤ ቀን ለርሱ የእሳት ዝርግ ተዘርግቶለት በርሷ በጀሃነም እሳት ውስጥ ሳይቃጠል የሚቀር የለም። ጎኑም፣ ግንባሩና ጀርባውም የሚተኮስ መሆኑ አይቀርም።" በቀዘቀዘች ቁጥር እየተመላለሰች መጠኑ ሀምሳ ሺህ አመት የሚያህል ለሆነ ቀን ይተኮሳል። ይህም በባሮች መካከል ፍርድ ተፈርዶ መንገዱ ወደ ጀነት ወይስ ወደ እሳት ነው የሚለውን እስኪመለከት ድረስ የሚዘልቅ ነው።" "የአላህ መልክተኛ ሆይ! ግመልስ?" ተባሉ። እርሳቸውም "የትንሳኤ ቀን በሆነ ጊዜ የተስተካከለ ሰፊ መሬት ላይ ባለቤቱ ተጥሎ ግመሏ ዱንያ ውስጥ ከነበረችበት የበዛች ሆናና ከነበሩት አንድም ግልገል ሳትቀነስ በሸኾናዋ የምትረግጠውና በአፏ የምትነክሰው ቢሆን እንጂ ሐቋን የማይወጣ የግመል ባለቤት የለም። ከሐቋ መካከልም ለመጠጥ በምትወርድበት ቀን አልቦ (ለሚስኪን ማጠጣት) ነው። የመጀመሪያዋ ባለፈችበት ቁጥር ሌላኛዋ እየተመላለሰች መጠኑ ሀምሳ ሺህ አመት የሚያህል ለሆነ ቀን ታሰቃየዋለች። ይህም በባሮች መካከል ፍርድ ተፈርዶ መንገዱ ወደ ጀነት ወይስ ወደ እሳት ነው የሚለውን እስኪመለከት ድረስ ነው።" አሉ። ለርሳቸውም "የአላህ መልክተኛ ሆይ! ከብትና ፍየልስ?" ተባሉ። እርሳቸውም "የትንሳኤ ቀን በሆነ ጊዜ የተስተካከለ ሰፊ መሬት ላይ ባለቤቱ በአፍጢሙ ተጥሎ ከነርሱም መካከል አንድም ሳይጎድልና አንድም ቀንዱ የተጠመዘዘ፣ ቀንድ የሌለው ወይም ቀንደ ሰባራ ሳይኖር እያንዳንዷ በቀንዷ የምትወጋው በጥፍሯም የምትረግጠው ቢሆን እንጂ ሐቋን የማይወጣ የከብትና ፍየል ባለቤትም የለም። የመጀመሪያዋ ባለፈችበት ቁጥር ሌላኛዋ እየተመለሰች መጠኑ ሀምሳ ሺህ አመት የሚያህል ለሆነ ቀንም ታሰቃየዋለች። ይህም በባሮች መካከል ፍርድ ተፈርዶ መንገዱ ወደ ጀነት ወይስ ወደ እሳት ነው የሚለውን እስኪመለከት ድረስ የሚቀጥል ነው።" አሉ። ለርሳቸውም "የአላህ መልክተኛ ሆይ! ፈረስስ?" ተባሉ። እርሳቸውም "ፈረስ ሶስት አይነት ነው። ለሰውዬው ወንጀል የሆነች፣ ሰውዬውን የምትሸሽገው የሆነችና ለሰውዬው ምንዳ የምታስገኝ የሆነች አለች። ለርሱ ወንጀል የሆነችበትማ ለይዩልኝ፣ ለፉከራና በሙስሊሞች ላይ ሊዘመትባት የታሰበችው ናት። እርሷ ለርሱ የምትሸሽግ የሆነችውም በአላህ መንገድ አስሯት ከዚያም በጀርባዋና በጫንቃዋ ላይ ያለውን የአላህን ሐቅ ያልረሳ ነው። ይህቺም እርሱን የምትሸሽግ ናት። እርሷ ለርሱ ምንዳ የምታስገኝ የሆነችው ደግሞ በአላህ መንገድ ለሙስሊሞች ሊዘምትባት በቡቃያ ስፍራ ወይም በጨፌ ውስጥ ያሰራት ነው። በዚህ ቡቃያ ስፍራ ውስጥ ወይም በጨፌ ውስጥ አንዳችም በበላች ቁጥር ምንዳ ለርሱ ቢፃፍለት፣ የእበቷና የሽንቷ ቁጥር ያህልም ለርሱ ቢፃፍለት እንጂ፤ የታሰረችበትን ገመድ አትቆርጥምም፣ ኮረብታን ወይም ኮረብታዎችን አትሮጥም አላህ በኮቴዋና በእበቷ ቁጥር ምንዳን ቢፅፍለት እንጂ፤ ባለቤቷ እርሷን ይዞ በወንዝ በኩል አያልፍምም እርሱ ሊያጠጣት ባይፈልግ እንኳ ከወንዙ አትጠጣምም አላህ ለርሱ በጠጣችው ቁጥር ምንዳ ቢፅፍለት እንጂ።" አሉ።
ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና የተለያዩ የገንዘብ አይነቶችንና የትንሳኤ ቀን ዘካቸውን ያላወጣ ሰው ምንዳ ምን እንደሆነ ገለፁ። የመጀመሪያው: ወርቅ፣ ብርና በነርሱ ደረጃ ያለ ገንዘብና መገበያያ ሸቀጥ ነው። ይኸውም ዘካ ግዴታ ሆኖበት ያልወጣለትን ወርቅና ብር ነው። የትንሳኤ ቀን ሲሆን በዝርግ መልኩ የሚቃጠልም የሚቀልጥም ይደረጋል። በጀሃነም እሳት ውስጥም ትቀጣጠላለች በርሷም ባለቤቱ ይቀጣበታል። በርሷም ጎኑም፣ ግንባሩና ጀርባውም ይተኮሳል። በቀዘቀዘች ቁጥር ግለቷ ይመለሳል። አላህ በፍጡራን መካከል ፈርዶ ከጀነት ነዋሪዎች ወይም ከእሳት ነዋሪዎች መካከል ከአንዱ እስኪሆን የአንዱ ቀን መጠን ሀምሳ ሺህ አመት የሚያህል በሆነበት የእለተ ትንሳኤ ሙሉ ጊዜው በዚህ ሁኔታ ቅጣቱ ይቀጥላል። ሁለተኛው: ግዴታ የሆነው ዘካዋንና ሐቋን ያልተወጣላት የግመል ባለቤት ነው። ከግመል ሐቅም እርሷ ዘንድ ለሚገኙ ድሆች በማለብ ማጠጣት ነው። ይህቺ ግመልም ተልቃ፣ ሰብታና ከነበሩበት ቁጥር በዝተው ይመጣሉ። የትንሳኤ ቀን የተስተካከለ ሰፊ መሬት ላይ ባለቤቱ ይዘረጋል፣ ይጣላል፣ ለርሷ ይለጠጣል። በእግሮቻቸውም ይረገጣል፣ በጥርሶቻቸውም ይነከሳል። የመጨረሻዋ ግመል ባለፈች ቁጥር የመጀመሪያው ይመለሳል። አላህ በፍጡራን መካከል ፈርዶ ከጀነት ነዋሪዎች ወይም ከእሳት ነዋሪዎች መካከል ከአንዱ እስኪሆን ድረስም የአንዱ ቀን መጠን ሀምሳ ሺህ አመት የሚያህል በሆነበት በእለተ ትንሳኤ ሙሉ ጊዜውን በዚህ ሁኔታ ቅጣቱ ይቀጥላል። ሶስተኛው: ግዴታ የሆነበትን ዘካ የማያወጣለት የከብት፣ የፍየልና የበግ ባለቤት የሆነ ሰው ነው። ከነበሩበት መጠን ምንም ሳይቀነስ በዝተው ይመጣሉ። የትንሳኤ ቀን የተስተካከለ ሰፊ መሬት ላይ ባለቤቱ ተዘርግቶ ይጣላል፣ ለርሷ ይለጠጣል። ከነርሱም መካከል ቀንዱ የተጠመዘዘ፣ ቀንድ የሌለውና ቀንዱ የተሰበረ አይኖርም። ይልቁንም የተሟላ ባህሪ ተላብሰው ነው የሚመጡት። በቀንዶቻቸውም ይወጉታል፣ በእግራቸውም ይረግጡታል። የመጨረሻዋ ባለፈች ቁጥር የመጀመሪያዋ ትመለሳለች። አላህ በፍጡራን መካከል ፈርዶ ከጀነት ነዋሪዎች ወይም ከእሳት ነዋሪዎች መካከል ከአንዱ እስኪሆን ድረስ የአንዱ ቀን መጠን ሀምሳ ሺህ አመት የሚያህል በሆነበት በእለተ ትንሳኤ ሙሉ ጊዜውን በዚህ ሁኔታ ቅጣቱ ይቀጥላል። አራተኛው: ፈረስ የሚያደልብ ነው። ይህም ሶስት አይነት ናቸው። አንደኛ: እርሷ ለርሱ ወንጀል የሆነችበት ናት። ይህም ለይዩልኝ፣ ለፉከራና ሙስሊሞችን ለመዋጋት የያዛት እንደሆነ ነው። ሁለተኛ: እርሷ ለርሱ የምትሸሽገው የሆነች ናት። ይህም በአላህ መንገድ ለመዋጋት የያዛት እንደሆነ ነው። ከዚያም ለፈረሷ በመቀለብ፣ ጣጣዋን በመቻል ከዚህም ውስጥ ኮርማዋን በማዘጋጀት ለርሷ መልካም የዋለ እንደሆነ ነው። ሶስተኛ: እርሷ ለርሱ ምንዳ የምታስገኝ የሆነች ናት። ይህም በአላህ መንገድ ለሙስሊሞች ለመዋጋት የያዛትና በቡቃያ ስፍራና በጨፌ ውስጥ ያሰማራት እንደሆነ ነው። ይህቺ ፈረስ አንድም አትበላም ለርሱ በበላችው ቁጥር ምንዳ ቢፃፍለት እንጂ፤ በእበቷና ሽንቷ ቁጥር ልክ ምንዳ ቢፃፍለት እንጂ፤ የምትታሰርበትን ገመድ ቆርጣ በምድር ከፍታ ላይ አትሮጥም አላህ ለርሱ በኮቴዋና እበቷ ቁጥር ልክ ምንዳን ቢፅፍለት እንጂ፤ ባለቤቱ እርሷን ይዞ በወንዝ በኩል ሲያልፍ እርሷን ማጠጣት ሳይፈልግም አትጠጣም አላህ በጠጣችው ቁጥር ለርሱ ምንዳ የሚፅፍለት ቢሆን እንጂ። ቀጥሎ ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሶላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና ስለአህያ እርሷም እንደ ፈረስ አምሳያ ናትን? ተብለው ተጠየቁ። እርሳቸውም: ከዚህች አጭር ከሆነችው አንቀፅ በቀር እርሷን የሚመለከት አንቀፅ አልወረደም። ይህቺ አንቀፅም ሁሉንም የአምልኮና የወንጀል አይነቶችን የምታጠቃልል ናት። ይህቺም አንቀፅ {የብናኝ ክብደት ያክልም መልካም የሰራ ሰው ያገኘዋል። የብናኝ ክብደት ያክልም ክፉን የሰራ ሰው ያገኘዋል።} [አዝዘልዘላህ:8] የምትለዋ የአላህ ንግግር ናት። አህያን ሲያደልብ አላህን ለመታዘዝ አልሞ ከሆነ የዚህን ምንዳ ያገኛል። ወንጀል ከሰራ ደግሞ የዚህን ቅጣት ያገኛል። ይህ አንቀፅ ሁሉንም ስራዎች የሚጠቀልል ነው።
ከዓዲይ ቢን ሓቲም (ረዲየሏሁ ዐንሁ) - አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸውና - እንደተላለፈው እንዲህ አሉ: «የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና እንዲህ ብለዋል: "ከናንተ መካከል በርሱና በአላህ መካከል አስተርጓሚ ሳይኖር አላህ የሚያናግረው ቢሆን እንጂ አንድም ሰው የለም ወደ ቀኝ ይመለከታል። ያሳለፈውን እንጂ ሌላ ምንም አይመለከትም። ወደ ግራም ይመለከታል ካሳለፈው በቀር ሌላ ምንም አይመለከትም። ከፊትለፊቱ ይመለከታል በፊትለፊቱ ከእሳት ውጭ ሌላ ምንም አይመለከትም። በተምር ክፋይ እንኳ ቢሆን እሳትን ተጠንቀቁ።"»
ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል።ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) ሁሉም አማኝ የትንሳኤ ቀን ብቻውን አላህ ፊት እንደሚቆምና አላህም ማንም በመካከላቸው ንግግሩን የሚተረጉም አስተርጓሚ ሳይኖር እንደሚያናግረው ተናገሩ። ከፊት ለፊቱ ካለችው እሳት ለመዳን የሚሄድበት መንገድ ያገኝ እንደሁ በሚል በድንጋጤ ብዛት ወደ ግራና ቀኝ አቅጣጫ እንደሚመለከትም ተናገሩ። ወደ ቀኝ አቅጣጫ ሲመለከትም ካሳለፈው መልካም ስራ በቀር ሌላ ምንም አይመለከትም። ወደ ግራ አቅጣጫ ሲመለከትም ካሳለፈው መጥፎ ስራ በቀር ሌላ ምንም አይመለከትም። ከፊትለፊቱ ሲመለከትም ከእሳት በቀር ሌላ ምንም አይመለከትም። በሲራጥ ላይ ማለፍ የግዱ ስለሆነበት እሳትን ወደ ጎን አድርጎ መተውም አልተቻለውም። ቀጥለውም ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈንና) የተምር ክፋይን የምታህል ትንሽ ነገር እንኳ በመመፅወት በናንተና በእሳት መካከል የሚከልል የመልካም ስራና የምፅዋት ጋሻ አዘጋጁ አሉ።